Wednesday, October 14, 2020

"የዛሬዋና የነገዋ ኢትዮጵያ ለወጣቶች ጥያቄ ምላሽ መስጠት የምትችል ሀገር እንትሆን በምክንያት እንተጋለን"

 በሀገራችን ለመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ ዋና ተዋንያን ህዝብ ሆኖ፤ ወጣቶች የአንበሳውን ድርሻ ይጋራሉ፡፡ ፍትሃዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት፣ ዲሞክራሲ፣ ነፃነትና እኩልነት በሀገራችን ለተመዘገበው ለውጥ ገፊ የትግል ማዕዘኖች ናቸው፡፡ 

 
ለውጡ ገና በዳዴ የሚድህ ቢሆንም በተፈለገው ፍጥነት መሔድ እንዳይችል በውስጥና በውጪ አርበኞች የሚገጥመው ፈተናም ቀላል ተደርጎ የሚወሰድም አይደለም፤ ወጣቶች ህይወታቸውን የሰጡለት ሀገራዊ ለውጥ እንዲያረጋግጥላቸው የሚፈልጉት ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲመጣ ቀጣይነት ያለው "በአመክንዮ የታገዘ ሞጋችነት" አማራጭ የሌለው ምርጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ 
 
የወጣቶችን ትዕግስት የሚፈታተኑ እዚህም እዛም ተጠራቅመው የቆዩና የታፈኑ በርከትከት ያሉ ጥያቄዎች መኖራቸው የማይካድ ሀቅ ቢሆንም፤ በነበራቸው የመሪነት "Statuesque" ያወረሱንን ጥያቄዎች በመኮርኮር ወጣቶችን የሁከት ዋና ተዋንያን ለማድረግ በጥፋት ሀይሉ ቢሞከረም "ለአይጧ ተብሎ ምጣድ እንደ ማይሰበር" በቂ ምላሽ አግኝተዋል፡፡ 
 
የሆነው ሆኖ "ለውጡን ጭራ ይዘናል ከያዝንም አንለቅም" ለውጡ ላይ የሚታየውን ጉድለት በማረም የዛሬዋና የነገዋ ኢትዮጵያ ለወጣቶች ጥያቄ ምላሽ መስጠት የምትችል ሀገር እንትሆን በምክንያት እንተጋለን፤ የወጣትነት ዘመናችንን ለመልካም ነገሮች ሁሉ ግባታ በማዋል ችግሮችን ተጋፍጠን ኢትዮጵያን እናንፃለን፡፡

Sunday, May 12, 2019


"ለማህበራዊ ፍትህና ዲሞክራሲ ዜጎች ታሪክ ሲሰሩ ታሪክ ሆነው አልፈዋል"
ሰላምና ዴሞክራሲን መገንባት በትውልድ ቅብብሎሽ እንጅ እንደ አጭር እርቀት እሩጫ በሰዓታት ልዩነት የሚጠናቀቅ አይደለም፡፡ በዲሞክራሲያዊ የመንግስት አስተዳደር ስርዓት የተሳካላቸው ሀገራት የመቶ አመታትን የዲሞክራሲ ሙከራ ጊዚያት አሳልፈው አሁን በዲሞክራሲ የመንግስት አስተዳደር ምሳሌ ለመሆን በቅተዋል፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ውድ ህይወታውን መሰዋታቸው ለማለት ያክል ሳይሆን በእኛ ዕድሜ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህና እኩልነት ታሪክ ሲሰሩ ታሪክ ሆነው አልፈዋል፡፡ ሆኖም መስዕዋት የተከፈለበት ተጋድሎ ከመስዕዋትነት ተርፈው ለወንበር ሲበቁ ሁሉም የህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች ወደ ኋላ ይተውና በቡድኖችና በግለሰቦች ፍላጎት የዜጎች ጥያቄ ይጠለፋል፡፡ ለዚህ የታሪክ አሻራ መረጃና ማስረጃ ማቅረብ ባይጠይቅም በአዎንታዊ ስኬታቸው ሲወደሱ በአሉታዊ ገፅታቸው በወከሉት ቡድን ስም ግለሰቦች ይዘረፋሉ፣ በወጡበት ብሔር ምክንያት ቱጃር እና ደሃ የሆኑበትን የታሪክ ክስተት ፅፈው አልፈዋል፡፡ ህሊና ላለው የህዝብ እንደራሴ ግን የወከለን ህዝብ በእኔ ስም ዝረፍልኝ፣ በእኔ ስም ሌላውን ባይተዋርና የበይ ተመልካች አድርግልኝ፣ በእኔ ስም ሌላውን አግለህ እኔን ብቻ ጥቀመኝ ብሎ አያቅም፡፡ የህዝብ ጥያቄ አንድና አንድ ብቻ ነው ማህበራዊ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ሰላም፣ ዲሞክራሲና ብልፅግና ከዚህ የተለየ ህዝብ እንደ ህዝብ ለመሪዎቹ ጥያቄ አቅርቦ አያቅም፡፡ ስለዚህ የህዝብ እንደራሴዎች ለህዝብ ጥያቄ ታማኝ በመሆነንና ባለመሆን ከህዝብ ጋር የምታደርጉት ግብግብ ዴሞክራሲን የመትከልና ለህዝብ ጥያቄዎች እንቅፋትም መሆናችሁን ልብ ሊሉ ይገባል፡፡

By:- አ ዕ ም ሮ